ከፓሪሽ አስተዳዳሪ እና መስራች የተላከ መልእክት

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ።
አንድነቱን በሦስትነቱ ሳንከፍል ሦስትነቱን በአንድነቱ ሳንጠቀልል፣ ሦስት አካላት አንድ መለኮት ብለን አምነን እናመልከው ዘንድ ከ4ቱ ባሕርያተ ሥጋ እና ከ3ቱ ባሕርያተ ነፍስ ግሩምና ድንቅ አድርጎ የፈጠረንን እግዚአብሔር አምላካችንን የባሕርይ ገንዘቡ በሆነው ምስጋና እናመሰግነዋለን፡፡
ወይእዜኒ አኃዊነ ፍቁራን ፍሥሐነ ወአከልነ ከመዝ ቁሙ ወጽንዑ በእግዚእነ ወመድኃኒነ፣ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ ደስታዬና ይልቁንም አከሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼና እህቶቼ በጌታችንና በመድኃኒታችን ጸንታችሁ ቁሙ። ፈልጵ 1፤1
የሰው ልጅ በጥንተ ተፈጥሮ በልዑል እግዚአብሔር እጆች ተሠርቶ ሁሉ ነገር በተከናወነበት እና በተሟላበት ዓለም ሲመጣ አንድ ትልቅ አደራ ተቀብሏል ይኸውም በኦሪት ዘፍ 2፡15 ላይ “እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ወስዶ ያበጃትና ይጠብቃት ዘንድ በኤደን ገነት አኖረው (አስቀመጠው) በሌላ አባባል አደራ ሰጠው ማለትም ይሆናል፡፡
እንግዲህ ከዚያ ጀምሮ የሰው ልጅ በነበረበት ዘመን ሁሉ ምድሪቱን ሲሠራ፣ሲያበጅና ሲገነባ ነው የኖረው። ይሁንና የበጎ ነገር ጠላት የሆነው ሰይጣን ደግሞ በብርቱዎች ጥንተ አደራ ተቀባዮች የታነፀውንና የተገነባውን በመናድና በማፍረስ የአንበሳ ድርሻውን ሲወስድ ኖሯል፡፡
እኛም እንግዲህ እግዚአብሔር ፈቅዶልን በጥንቱ አደራ መሠረት እናበጀውና እንጠብቀው ዘንድ ይህንን ታላቅና ሠፊ መሬት ሰጥቶናል፣ ብንሠራበት ራሳችንንም መጪውንም ትውልድ እንጠቅምበታለን፣ ገነት መንግሥተ ሰማያትንም እንርስበታለን፡፡
ከቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ምhንያት ብንወጣም እግዚአብሔር በባዕድ አገር ይህንን የሚያህል ቦታና ቤት የሰጠን ያለምንም ድካምና ጥረት ይሁን እንጂ የሰጠበት የራሱ የሆነ ዓላማ ግን አለው፥ ይኽውም በማቴ 25፡14 ጀምሮ እንደተመዘገበው አትርፈንበት እንድንመሰገንበት፣ ማለትም ታማኝ አገልጋዮች ሆይ በዚህ በጥቂቱ ታምናችኋልና ሁሉም በተሟላበት በመንግሥተ ሰማያት እሾማችኋለሁ፣ ወደ ጌታችሁ ደስታ ኑ ግቡ እንድንባልበት በመሆኑ ነቅተንና ተግተን የተሰጠንን አደራ እንወጣ በማለት እያሳሰብኳችሁ፣ እስካሁን በተሠራው መንፈሳዊ ተግባር ሁሉ ሁላችሁም ይህ ተግባር የኔም፣ የልጆቼም፣ ይልቁንም የቅድስት አገሬ ኢትዮጵያና የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያኔ ነው ብላችሁ በጸሎት፣ በምክር፣ በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በጉልበት ላደረጋችሁት ኀብረትና ድጋፍ ከልብ የመነጨ፣ ፍቅር የሞላበት ምስጋናዬን እያቀረብኩላችሁ መልዕክቴን በዚሁ አጠቃልላለሁ፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ከቡር አሜን።